በአማራ ክልል መማር ማስተማርን የሚመጥን ደረጃ ያላቸው ት/ቤቶች ከ17 በመቶ አይበልጡም ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በክልሉ ለትክክለኛ መማር ማስተማር የሚመጥን ደረጃ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ከ17 በመቶ እንደማይበልጡ ገለጹ፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ሕዝባዊ የንቅናቄ መድረክ በባሕርዳር ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ÷ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ትልቁ አቅማችን ትብብራችን ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ስለሆኑ÷ ሕዝቡ፣ ባለሃብቶች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቀርበዋል፡፡
በመምህራን ሥልጠና ረገድ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ማለታቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ካለው ሰፊ የመልማት ፍላጎት አንጻር ለትምህርት ቤቶች ደረጃ መሻሻል እና ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በርካታ ባለሃብቶች በግል ተነሳሽነት ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ገንብተው ለትውልድ ማበርከታቸውን ጠቅሰው÷ ሌሎች ባለሃብቶችም እንደዚህ አይነት የማይዘነጋ በጎ ተግባር እንዲፈፅሙ ጠይቀዋል፡፡