Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት መሰረተ ልማት ማሻሻያ ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ የትምህርት መሰረተ ልማት ማሻሻያ ንቅናቄ ዛሬ ተጀምሯል።

በንቅናቄው ማስጀመሪያ ላይ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋው በችግሩም 287 ትምህርት ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ከዚህም ውስጥ 196 የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶቹን መልሶ ለመገንባት ከ7 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ በጥናት መረጋገጡንም አመልክተዋል።

የትምህርት ተቋማት ደረጃ ለትምህርት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ-መስተዳድሩ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቆ መልሶ ለመገንባት እና የሌሎቹን ደረጃ ለማሻሻል ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው÷ በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች ቢሰሩም ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የተደረጉ ጥረቶች ግን ተፈላጊው ውጤት አልተመዘገበባቸውም ብለዋል።

የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል ወሳኙ ጉዳይ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ማሻሻል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም እንደ አገር በሁሉም ክልሎች ንቅናቄ በመካሄድ ላይ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የትምህርት ቤቶችን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ለማሻሻል መንግስት ብቻውን ሊፈጽመው እንደማይችል ጠቁመው፣ መላው ሕዝብ ለትምህርት መሰረተ ልማት መሻሻል ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ በበኩላቸው÷ በጸጥታ ችግር ምክንያት በትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት በ2015 ዓ.ም ትምህርት መማር የነበረባቸው 50 ሺህ ገደማ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.