የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ሎጂስቲክስ ዘርፉን ተጠቃሚነት የሚያጠናክር ቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቋመ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ሎጂስቲክስ ዘርፉን ተጠቃሚነት የሚያጠናክር ቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
የቴክኒክ ኮሚቴው የዘርፉን ችግሮች በጋራ በመፍታት ተጨማሪ የውጤት ዕድሎችን መፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።
ላለፉት ሁለት ቀናት በጂቡቲ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የኢትዮ ጂቡቲ የቢዝነስ ማስፋፊያ ጉባዔ ተጠናቋል።
አዲስ አበባ የተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ጉባዔ ክፍተቶችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የዳሰሰ ሲሆን÷ በሁለተኛው ዙር ይህንን በመገምገምና አቅጣጫ በማስቀመጥ የሚከታተለውን የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሟል።
የቴክኒክ ኮሚቴው በሁለቱም ሀገራት ከሎጂስቲክስ ዘርፉ ጋር ትስስር ካላቸው ተቋማት የተውጣጣ ነው።
የዘርፉን ጤናማነት በመጠበቅ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በማስታጠቅ እና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ለሌሎችም ዘርፎች እንዲተርፍ ማድረግ እንደሚገባ በመድረኩ ተጠቅሷል።
በአሸናፊ ሽብሩ