Fana: At a Speed of Life!

2 ሺህ 300 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከ2 ሺህ 300 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን የክልሉ ሕብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ሃላፊ መስፍን ረጋሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷  ሕገ-ወጦች በክልሉ የተፈጠረውን የማዳበሪያ እጥረት ባልተገባ መልኩ በመጠቀም  እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

በዚህም ከ2 ሺህ 330 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መያዙን ጠቁመው÷ በድርጊቱ የተሳተፉ 30 ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉንም አንስተዋል።

በክልሉ በዘርፉ የሚፈፀመው ሕገ -ወጥነት የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ያስከተለ ሲሆን÷ አርሶ አደሮችም ማዳበሪያ በኩንታል እስከ 11 ሺህ ብር ለመግዛት መገደዳቸውን አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው÷ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሕገወጦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከችግሩ ስፋት አንፃር አሁንም ያልተደረሰባቸው መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ም/አስተዳዳሪ ተካልኝ ይማሙ ÷የዞኑ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጭምር በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው እርምጃ መውሰዱን አረጋግጠዋል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.