Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ የንግዱን ማሕበረሰብ የሚያስፈራሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግዱን ማህበረሰብ በማስፈራራት የተሰማሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አሳስቧል፡፡

አገልግሎቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን (ንብረት) ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎች የአንድ ሀገር የፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማና የተረጋጋ እንዳይሆን ያደርጋሉ ብሏል፡፡

በተጨማሪም በሀገር ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ስምምነት ተደርሶበት ሀገራት በጋራና በተናጠል ወንጀሎቹን የመከላከልና መቆጣጠር እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አንስቷል፡፡

ኢትዮጵያ  የዚሁ ስምምነት አካል በመሆኗ ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች ያለው መግለጫው÷ በዚህም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጿል።

የወንጀል ድርጊቶቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአዋጅ ቁጥር 780/2005 መሰረት ለሪፖርት አቅራቢ፣ ለህግ አስከባሪ እና ተቆጣጠሪ ተቋማት ግልጽ ስልጣንና ተግባር ተሰጥቶ እየተሰራ  እንደሚገኝም ጠቁሟል።

ሆኖም ግን አንዳንድ ግለሰቦች ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ራሳቸው ሀሰተኛ የማደናገሪያና ማስፈራሪያ ስልቶችን በመጠቀም የንግዱን ማህበረሰብ በማሸበር በህገ-ወጥ መንገድ ለመጠቀም እንቅስቃሴ የማድረግ ዝንባሌዎች እንዳሉ ማወቅ መቻሉን አብራርቷል፡፡

እነዚህ ግለሰቦች አገልግሎቱ በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ላይ ዕግድ ሊጥል እንደሆነ በማስመሰል፣ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማቀነባበር፣ በማዘጋጀትና በመንዛት የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለማስፈራራትና በወንጀል ድርጊት ተጠቃሚ ለመሆን የሚሞክሩ መሆናቸውን መገንዘብ መቻሉን ገልጿል።

ወንጀሎቹን የመከላከልና መቆጣጠር ሂደት ውስጥ ህብረተሰቡን ጨምሮ ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የየራሳቸው ድርሻ ያላቸው መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡

ስለሆነም የንግዱን ማህበረሰብ በማስፈራራት በወንጀል ድርጊት ለመጠቀም የሚሞክሩ ግለሰቦችን ከተመለከቱ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በስልክ ቁጥር 011-812-8261 በመጠቆም የድርሻቸውን እንዲወጡ አገልግሎቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በዚህ የወንጀል ድርጊት ያለ አግባብ ለመጠቀም በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦችም ከወንጀል ድርጊታቸው እንዲትታቀቡ  አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.