አዘርባጃን በመንግሥት ኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች ላይ ኢትዮጵያን እንደምትደግፍ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዘርባጃን በመንግሥት ኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች ዲጂታይዜሽን ላይ ልምዷን ለማካፈልና ኢትዮጵያን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በአዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስና ሶሻል ኢኖቬሽን ኤጀንሲ ሹም ኡልቪ መሕዲየቭ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ በአዘርባጃን 400 የሚደርሱ የመንግስት አገልግሎቶችን ለዜጎች ባሉበት ማቅረብ መቻሉ ተነስቷል፡፡
በኢትዮጵያም ከ300 በላይ አገልግሎቶችን ለዜጎች ባሉበት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ስለመሆኑ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) መናገራቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የአዘርባጃን ባለሃብቶችም የቴክኖሎጂ ስታርታፖችን ለመደገፍ በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኡልቪ መሕዲየቭ በበኩላቸው÷ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ለዜጎች በማድረስ ያላትን ልምድ ለማካፈልና ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ አዘርባጃን ቁርጠኛ ናት ብለዋል፡፡
አዘርባጃን በተመድ የተመሰከረላትን ልምዷን ለኢትዮጵያ ለማካፈልና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል፡፡
የአዘርባጃን ባለሃብቶችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም ወደ ትግበራ የሚያስገቡ አሰራሮችን በጋራ በመቅረጽ ምቹ እድሎቹን ለመጠቀምና ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ ለመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አዘርባጃን የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታይዝ ካደረጉ የዓለም 100 አገራት ተቀዳሚ በመሆን በተባበሩት መንግሥታት የእውቅና የምስክር ወረቀት አላት፡፡