የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መርህ የኢትዮጵያን መሰረታዊ ጉዳዮች በማቀንቀን ላይ የተመሰረተ ነው – ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋና መርህ የኢትዮጵያን መሰረታዊ ጉዳዮች በማቀንቀን ላይ የተመሰረተ ነው አሉ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባለፉት ዓመታት ሲያከናውናቸው በነበሩ ሰፋፊ ተግባራት ከተቋሙ ጋር በጋራ ሲሰሩ ለነበሩ አካላት የምስጋና መርሐ ግብር አዘጋጅቷል፡፡
ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሁለት ሚዲያዎች ተዋህደው ወደ አንድ የመጡበት መንገድ የኢትዮጵያን መሰረታዊ ጉዳዮች የማቀንቀን ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማጽናት፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር፣ ገዢ የወል ትርክትን እንዲሁም ኢትዮጵያ የምትበለጽግበትን እሳቤ በማህበረሰቡ ውስጥ ማስረጽ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መርህ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህንን መርህ እውን ለማድረግና ተቋሙን ለማሳደግ የሚያቀርባቸውን ይዘቶችና የተቋሙን የአሰራር ስርዓት፣ የስራ ከባቢ እንዲሁም ግብዓቶች አጣጥሞ መጓዝ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጉዞ የኢትዮጵያ የሚዲያ ጉዞ አካል መሆኑን ጠቅሰው፥ ለህዝቡ ተደራሽ የሚያደርጋቸውን ይዘቶችና የተቋሙን አሰራርና የሥራ ከባቢ በማሻሻል ረገድ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ ከተቋሙ ጋር ተቀራርበው እየሰሩ የሚገኙ አካላት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ገልጸው፥ የጋራ ግባችን አንድ በመሆኑና ያለችን አንዲት ሀገር በመሆኗ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሀገሪቱ የጉዞ መስመር እየተጓዘ ይገኛል ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፥ የተቋሙ አጋር አካላት ባለፉት ጊዜያት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም ተቋሙ አሰራሮቹንና ይዘቶቹን በማሻሻል ይበልጥ የተሻለ የሚዲያ ተቋም ለመሆን ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡