Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ እና ደቡብ ኮሪያ በኡጋንዳ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎችን ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ እና ደቡብ ኮሪያ በቅርቡ በሀገሪቱ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎችን መገንባት እንደሚጀምሩ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ አስታውቀዋል።
ከ25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች እና ልዑካን በተገኙበት 2ኛው የቡድን 25 አፍሪካ ቡና የመሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ባደረጉት ንግግር የኒውክሌር ሃይል ማመንጫ በሀገሪቱ ለመገንባት ከሩሲያ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ስምምነት መደረጉን ጠቁመዋል።
ሩሲያ እና ደቡብ ኮሪያ 15 ሺህ ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ሁለት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎችን እንደሚገነቡ ነው የተናገሩት።
የኒውክሌር ኘሮጀክት ግንባታው ሚከናወነው ሀገራት ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት የኃይል ደህንነትን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚችሉ በሚያስቡበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር ኡጋንዳ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት የሚያስችል የውሃ ሃብት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
ይሁንና በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመዳሰስ ተጨማሪ ትብብር እንደሚያስፈልግ እና በዚህም የኒውክሌር ሃይልን ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአየር ንብረቱ እየተቀያየረ በመምጣቱ የውሃ ሃይል አስተማማኝ አለመሆኑንም መጠቆማቸውን አናዱሉ ዘግቧል።
ባለፈው ወር በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ኡጋንዳ እና ሩሲያ በኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይ ስምምነት መፈራረማቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በኡጋንዳ የኃይል እና ማዕድን ልማት ሚኒስቴር በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ከፍተኛ መጠን ያለው የዩራኒየም ክምችት እንደሚገኝ ማጥናቱን ተከትሎ የኒውክሌር ሀይልን ማምረት እንደምትችል አረጋግጧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.