ጣሊያን በአውሮፓና አፍሪካ መካከል ድልድይ በመሆን ትብብሮችን ታጠናክራለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ሀገራቸው በአውሮፓና አፍሪካ መካከል እንደ ድልድይ በመሆን የፖለቲካ ትብብርን በማጠናከር የአፍሪካ ኅብረትን እንቅስቃሴዎች ትደግፋለች አሉ።
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጣሊያን በጉባኤው ላይ መሳተፏ ታሪካዊ ዕድል ነው መሆኑን ገልጸው፥ ይህንን ዕድል በጠንካራ የኃላፊነት ስሜት እንደሚቀበሉት ተናግረዋል።
ጣሊያን አፍሪካ ቅድሚያ በምትሰጣቸው ጉዳዮች ላይ አስተዋፅዖ ለማድረግ የነደፈችው “የማቲ ፕላን” ለአፍሪካ የመሰረተ ልማት፣ ግብርና፣ ጤና፣ ውሃ እና የሙያ ስልጠናዎችን የሚሸፍን የኢንቨስትመንት ተነሳሽነት እንደሆነ አስረድተዋል።
ዕቅዱ ከአፍሪካ ህብረት የረጅም ጊዜ የልማት አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸው፥ ጣሊያን ከዓለም አቀፍ የንግድ አውታሮችና አጋሮች ጋር በመተባበር ለአፍሪካ የገበያ ትስስርና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ አድርጋለች ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለአፍሪካ ወጣቶች ዘላቂ የስራ እድል በሚፈጥሩ የትምህርት፣ የሙያ ስልጠና፣ ፈጠራና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ጣሊያን በሰውሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚሰጡ የስልጠና መርሐ ግብሮችን እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል፡፡
ጣሊያን እና አውሮፓ ያለ አፍሪካ የወደፊት እድላቸውን ማቀድ አይችሉም በማለት የአፍሪካ ዓለም አቀፋዊ ሚና ወሳኝ መሆኑንም ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፥ ማንኛውም ትብብር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ እንጂ በበጎ አድራጎት መሆን የለበትም ነው ያሉት፡፡
ጉባኤው በአፍሪካና አውሮፓ ግንኙነት ላይ አዲስ ምዕራፍ ለመቅረጽ እንደሚያስችል ጠቅሰው፥ በምርምር፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በፈጠራና ክህሎት ዘርፍ ጠንካራ ጥምረት እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የጣሊያን-አፍሪካ ስብሰባ በማዘጋጀቷ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
በሶስና አለማየሁ