አምባሳደር ኤል አሚን ሱውፍ በሶማሊያ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን አመሰገኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተወካይ አምባሳደር መሃመድ ኤል-አሚን ሱውፍ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ሶማሊያን ለማረጋጋት ላደረጉት አስተዋፅዖ አመስግነዋል፡፡
በሶማሊያ ባይደዋ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ግዳጃቸውን የፈፀሙ የኢትዮጵያ ወታደሮች የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ሽኝት እና የሜዳይ ሽልማት ስነ-ስርዓት ተደርጎላቸዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ በሶማሊያ የደቡብ ምዕራብ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲአዚዝ ሀሰን መሃመድ ፣ በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሃመድ ፣የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይል አዛዥ ሌ/ ጀ ሳም ኦኪዲንግና ሌሎች ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል፡፡
በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተወካይ አምባሳደር ኤል አሚን ሱውፍ÷ “ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን ላሳያችሁት ትጋትና ቁርጠኝነት አመሰግናለሁ” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮች ባደረጉት ድጋፍ መሰረት አሁን ላይ ሶማሊያ እንደ አልሸባብ ያሉ አሸባሪዎችን ለመዋጋት ከፍተኛ አቅም መፍጠሯን አምባሳደሩ አብራርተዋል፡፡
በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሙሃመድ በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ መሆነኗን ገልፀዋል፡፡
በሀገሪቱ ቤይ ፣ባኮልና ጊዶ የተባሉ ክልሎች በአፍሪካ ህብረት ሰላም ማስከብር ተልዕኮ ስር በኢትዮጵያውያን ወታደሮች ሲጠበቁ የነበሩ አካባቢዎች መሆናቸውን የህብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡