በካናዳ የተከሰተው ሰደድ እሳት ከ30 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቀለ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በካናዳ ሰደድ እሳት በመቀስቀሱ ከ30 ሺህ የሚልቁ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው መፈናቀላቸው ተሰማ፡፡
ሰደድ እሳቱ ሰፊ የካናዳን ክፍል መሸፈኑም ነው የተገለጸው።
በመጠኑ ትልቅነት እንዲህ ያለ አደጋ በካናዳ ከዚህ በፊት ተከስቶ እንደማያውቅም ተዘግቧል፡፡
የሀገሪቷ መንግስት አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁንም ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ 36 ሺህ ያኅል ሰዎች የአደጋው ሰለባ ሳይሆኑ እንደማይቀርና በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆኑ እንደተነገራቸውም ተጠቁሟል፡፡
በተያያዘ ዜና በፔሩ ደቡባዊ ቀጣና በተቀሰቀሰው ከባድ ሰደድ እሳት ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሕይወታቸውን ሳያጡ እንዳልቀረ ፣ 12 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰ ብሎም ተጨማሪ ሁለት ሰዎች የገቡበት እንዳልታወቀ ተዘግቧል፡፡
በአርጀንቲና የተከሰተው ሰደድ እሳት በመባባሱም የአካባቢው ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል ነው የተባለው፡፡
ከደቂቃዎች በፊት ኢንዲፔንደንት ቲ.ቪ የሀገሪቷ የዓየር ትንበያ አገልግሎት ዋቢ አድርጎ ባስመለከተው ዘገባ ሰደድ እሳቱ በከፍተኛ አውሎ ንፋስ ታግዞ አድማሱን ማስፋቱ ለአደጋው አሳሳቢነት ዓብይ ምክንያት ሆኗል ብሏል፡፡
የሀገሪቷ የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ÷ ከ2000 ሜትር በላይ የፋይበር ኦፕቲክስ መሥመር በሰደድ እሳቱ መውደሙን ጠቁሟል፡፡