ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከሚካሄደው የBRICS-Africa Outreach እና BRICS Plus ስብሰባ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
መሪዎቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ የበለጠ ትስስር ለመፍጠር ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)÷ ቻይና ላለፉት ዓመታት ለምታደርግላት ከፍተኛ ድጋፍ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች ብለዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት ለብዙ ዘርፎች ለጋራ ዕድገትና ልማት ጠንካራ መሰረት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነትን ለማጠናከር ያለንን ቁርጠኝነት ለፕሬዚዳንት ሺ በድጋሚ ገልጨላቸዋለሁ ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ ሀገራዊ ልማትን በመምራት ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) አመራር አድንቀዋል፡፡
እንዲሁም በሰላምና በልማት ጥረቶች፣ በመልሶ ግንባታው ዘር፣ ኢንቨስትመንቶችን እና የንግድ ግንኙነቶችን በማጎልበት ረገድ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
በጋራ ማዕቀፍ ስምምነት መሰረት ቻይና ለኢትዮጵያ በፈረንጆቹ በ2023/2024 ጊዜ ውስጥ ለደረሰ የዕዳ ክፍያ እፎይታ እንደምትሰጥ ፕሬዚዳንት ሺ አመላክተዋል፡፡