የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከበረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከብሮ ተጠናቀቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እንዳስታወቀው፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር ተከብሮ ተጠናቅቋል።
ተቋሙ ከሌሎች የጸጥታና ደኅንነት ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፖሊስ ሠራዊት በማሰማራት፤ ከህዝብ፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎችና ከወጣቶች ጋር ተባብሮ በመስራቱ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስችሏል፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረገው ህዝብ እንዲሁም ለሀይማኖት መሪዎች፣ ለበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ ለወጣቶች እና በተለይ የተሰጣቸውን ግዳጅ በሚገባ ለተወጡት የፀጥታና ደኅንነት ኃይሎች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል።
ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ እያሳየ ያለውን ቀና ትብብር በቀጣይ በሚከበሩት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆረ አርሰዲ የኢሬቻ በዓላት ላይም በተመሳሳይ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።