የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀብሎ ማፅደቁ ለሀገራችን ታሪካዊ ሁነት ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀብሎ ማፅደቁ ለሀገራችን ታሪካዊ ሁነት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉን አካታችና ብልጽግና የሰፈነበት ዓለም አቀፋዊ ስርዓትን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የራሷን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ናት ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀብሎ ማፅደቁ ለሀገራችን ታሪካዊ ሁነት ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ ጉባኤ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀብሎ ማፅደቁ ለሀገራችን ታሪካዊ ሁነት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች ለሚሆን የበለፀገ የዓለም ስርዓት መስፈን ከሁሉም ጋር ለመስራት ሁሌም ዝግጁ ናት ሲሉም አረጋግጠዋል።
15ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያን በአዲስ አባልነት መቀበሉ ይታወሳል።
ጉባኤው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ አርጀንቲና፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች እና ግብጽን በአዲስ አባልነት ተቀብሏል።
ብሪክስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ላይ ካሉ የስብስብ ኃይሎች መካከል÷ በሕዝብ ብዛት፣ በኢኮኖሚ እና በመደመጥ አቅሙ እያደገ የመጣ ቡድን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ይህ ቡድን እያደገ ከመጣ በኋላ ከ40 የማያንሱ ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ፍላጎት አሳይተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከእነዚህ ውስጥ 6 ሀገራት በአሁኑ መመዘኛ አሟልተው የብሪክስ አባል መሆን ችለዋል ነው ያሉት።
ይህ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎም ለአፍሪካ ትልቅ ኩራትና የዲፕሎማቲክ ድል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ስትመረጥ ታሪኳ፣ የሕዝብ ብዛቷ በተለይም አሁን ላይ በዓለም ላይ ከፍተኛ ዕድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ በእነዚህ ሀገራት ስለታመነበት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የታዳሽ ኃይል ልማት፣ በግብርና ምርት እራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲሁም አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂ ዲ ፒ) ዕድገት በዓለም ላይ በቁጥር ከሚጠቀሱ ከፍተኛ ዕድገት ካመጡ ሀገራት አንዷ በመሆኗ ኢትዮጵያ የመደመጥ አቅሟ እያደገ በመምጣቱ ሀገሪቱን ማስገባት የደቡብ – ደቡብ ትብብርን ዕውን ያደርገዋልም ነው ያሉት።
የደቡብ-ደቡብ ትብብር ኢትዮጵያ በሌለችበት ሙሉ አይሆንም በሚል አብዛኛው ባላቸው የጂ ዲ ፒ አቅም ከፍ ያሉ ሀገራት የተወሰዱ ቢሆንም፥ ኢትዮጵያ ባላት የዕድገት ተስፋና አጠቃላይ ሂደት ለመመረጥ በቅታለች ብለዋል።
“ብዙዎች ለመካተት የሚፈልጉበት መድረክ ነው፤ በብዙ ትግል፤ በብዙ ንግግር የተገኘ ድል ነው፤ ለዚህም ቻይናን በብዙ እናመሰግናለን፤ ከፍተኛ ዕርዳታ አድርጋልናለች” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
እንደዚሁም፥ የቡድኑ አባል ሀገራት የሆኑትን ሕንድ፣ ሩሲያ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካን ኢትዮጵያ ታመሰግናለች ብለዋል።