Fana: At a Speed of Life!

የሕብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት መረባረብ ይገባል – ከንቲባ ከድር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አመራሩና ሠራተኛው በቅንነትና ታማኝነት በማገልገል የሕብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት እንዲረባረብ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አሳሰቡ።

በአስተዳደሩ በሚገኙ የመንግስት ተቋማት “ኢትዮጵያን እናገልግል” በሚል መሪ ሐሳብ የአገልጋይት ቀን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ተከብሯል።

በአቶ ከድር የተመራ የአስተዳደሩ የካቢኔ አባላትና አመራሮችን ያካተተ ቡድን በድሬዳዋ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን፣ በድል ጮራ ሪፈራል እና በሳብያን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ተገኝቶ ህሙማንን የመጠየቅና የመንከባከብ ሥራ አከናውነዋል።

እንዲሁም በአስተዳደሩ የትራንስፖርት ዘርፉን ከሚመሩ ተቋማት ጋር ሕዝብን በቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል ቃል በመግባት ቀኑ መከበሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከንቲባ ከድር ጁሃር በቀኑ አከባበር ላይ እንዳሉት÷ ሕዝብን በታላቅ ክብርና ትኅትና ማገልገል የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማፅናትና ኢትዮጵያን ማክበር ነው።

በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ሠራተኞችም ሕዝብን በትኅትና በማገልገል የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መረባረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሕዝብ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚያነሳቸውን ችግሮች በተቀናጀ መንገድ መፍታት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ በተሻለ ውጤት ማጀብ ነው ብለዋል ከንቲባው።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው÷ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተከናወነው ሪፎርም የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ 165 አገልጋዮች ዕውቅና መሠጠቱም ተመላክቷል፡፡

ተሸላሚዎች ሕዝብን ይበልጥ በአርዓያነት በማገልገል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.