ከ40 አመታት በላይ ላገለገሉ መምህራን የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ40 አመታት በላይ በማስተማር ሙያ ላገለገሉ መምህራን የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልቃድርን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
እንዲሁም ከ40 አመታት በላይ ያስተማሩና በማስተማር ሙያ ላይ የሚገኙ መምህራን ታድመዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአንጋፋ መምሕራን ሽልማት በሰጡበት ወቅት ባስታለፉት መልዕክት÷ መምህራኖቻችን ሁላችንንም የቀረጹ ናቸው፣ መነሻችን ትምህርት ቤት ነው ብለዋል፡፡
በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ከራሳቸው በላይ ለሌሎች አገልግሎት የኖሩትን ማመስገን እንደሚገባም አመልክተዋል።
ማገልገል ክብርም፣ መታደልም እንደሆነ ገልጸው፤ ለማገልገል ቅንነትና ዝቅ ማለት እንዲሁም ራስን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አሊ ከማል በበኩላቸው÷ በአገልጋይነት ቀን ቢሮው ዜጎችን በማስተማርና ትውልድን በመቅረጽ አስተዋጽኦ ላደረጉ መምህራን ያለውን ክብር ለመግለጽ መርሐ ግብሩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
152 መምህራንን ለማድነቅ፣ ለማመስገን እንዲሁም እውቅና ለመስጠት መርሐ ግብሩ እንደተዘጋጀ ጠቅሰዋል።
መምህራን ተማሪዎች አለምን እንዲዞሩ፣ በእውቀት ከአድማስ አድማስ እንዲበሩ፣ እንደ ወርቅ በፈተና ነጥረው እንዲከብሩ እንዲሁም በራስ መተማመንን በማዳበር በማንነታቸው እንዲኮሩ ለማድረግ ብዙ ዋጋ ስለሚከፍሉ ዕውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
የእውቅና እና የምስጋና ፕሮግራሙ ቀጣይ ለሚሰሩ የትምህርት ልማት ስራዎች ስንቅ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።
በዛሬው የእውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር ከ40 ዓመት በላይ ላገለገሉና ከየክፍለ ከተሞቹ ለተውጣጡ አንጋፋ መምህራን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሽልማት ሰጥተዋል፡፡
በየሻምበል ምሕረት