ብልጽግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደርበትን የምርጫ ምልክት ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደርበትን የምርጫ ምልክት ይፋ አድርጓል፡፡
ፓርቲው “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ የማኒፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ በዋና ጽ/ቤቱ እያካሄደ ይገኛል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አደም ፋራህን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ብልጽግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሕዝብ ይሁንታ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገር ግቡ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት የፓርቲው የምርጫ ምልክት “የስንዴ ነዶ” ሆኖ የተዋወቀ ሲሆን ምልክቱም የመደመር፣ የትብብር እና የአንድነት ምልክት መሆኑ ይፋ ተደርጓል፡፡
“ትናንትን ማከም ነገን መተለም” በሚል ፓርቲው በአራት ዘርፎች የሚተገብራቸው የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ዘርፎችን አብራርተዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ በአጠቃላይ 169 ገጾች ያሉት የምርጫ ማኒፌስቶውን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ገጾቹም በቀጣይ አምስት አመታት የሚተገበሩ 15 አምዶችን መያዙ ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም ጠንካራና ቅቡልነት ያለው መንግስት መገንባት፣ በተለያዩ አካባቢ የሚታዩ ግጭቶችን መፍታት፣ የኢትዮጵያ የተፅዕኖ አድማስ ማስፋት እንዲሁም የዴሞክራሲ ፖለቲካን ባህል መገንባት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በሰለሞን በየነ