ባለፉት ወራት ከታየው ሙቀት የከፋ የአየር ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ተመድ አስጠነቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ወራት ከታየው ሙቀት የከፋ የአየር ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል በተባበሩት መንግስታት የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
ከአስከፊ የበጋ ሙቀት በኋላ በዓለም ሌላ ከባድ የአየር ንብረት መዛባት መጀመሩንም አመላክቷል።
የፈረንጆቹ 2023 ሐምሌና ነሐሴ ወራት እጅግ ሞቃታማ ወር ሆነው መመዝገባቸውን ያስታወሰው ድርጅቱ፤ ከአውሮፓ ህብረት ኮፐርኒከስ የአየር ንብረት ለውጥ አገልግሎት ያገኘው መረጃ የከፋ የአየር ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ፍንጭ ስለመስጠቱ ገልጿል።
የነሐሴ ወር በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ በማለት ወደ 21 ዲግሪ ሴልሺየስ በመጠጋት ከፍተኛው የዓለም አማካይ ወርሃዊ የሙቀት መጠን እንደታየበት ነው የተጠቆመው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሪፖርቱ ከተለቀቀ በኋላ በሰጡት መግለጫ “የበጋው አየር ሙቀት ብቻ ሳይሆን እጅግ የበረታ ሙቀት ነበር” ብለውታል።
እንደ አውሮፓ ህብረት የአየር ንብረት ለውጥ ገለፃ የፈረንጆቹ 2023 ከፍተኛ ሙቀት የተስተናገደበት ዓመት ሆኗል።
የሚስተዋለውን የአየር ንብረት መዛባት እና ያንን ተከትሎ ለተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት የሰው ልጅ ለአካባቢ ጥበቃ የሰጡት ትኩረት አናሳ መሆን እንደሆነ ተገልጿል።
ሰዎች ከሰል፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ በመጠቀም ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት ካርበን እና የተፈጥሮ አየር መዛባት መከሰት ለከፍተኛ ሙቀት መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸው ተጠቁሟል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ የዓለም አየር እና ውቅያኖሶች ከፍተኛ ሙቀት ሲያስመዘግቡ የአንታርክቲክ ባህር የበረዶ ግግር መጠን መቀነሱን ቀጥሏል ሲል የዓለም የሜቲዎሮሎጂ ድርጅትን ዋቢ አድርጎ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!