Fana: At a Speed of Life!

በሐረር በእሳት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ግብረ ሃይል ተቋቋመ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) በሐረር ከተማ በተከሰተ እሳት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን መልሶ ማቋቋም የሚያስችል ግብረ ሃይል አቋቁሟል፡፡

በሐረር ከተማ ሸዋ በር አካባቢ በተለምዶ “ታይዋን” ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ሌሊት 10 ሰዓት ላይ የደረሰ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ÷ አካባቢው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ እና ለብዙ ነዋሪዎች የገቢ ምንጭ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በእሳት አደጋው በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውንም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

የእሳት አደጋውን አስመልክቶም የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በውይይቱም በአፋጣኝ የአደጋውን መንስኤ እና የደረሰውን የጉዳት መጠን በማጥናት በአካባቢው ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚሰራ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

መስተዳድር ምክር ቤቱ ከደረሰው የእሳት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ሦስት የተለያዩ ግብረ ሃይሎችን አቋቁሟል።

በዚህ መሰረትም የአደጋውን መንስኤ የሚያጣራ፣ የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያጠና እና በአካባቢው ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ግብረ ሃይል አቋቁሟል።

የክልሉ መንግስት በቃጠሎው ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች መልሶ ለማቋቋም በሚያከናውነው ስራ ሕዝቡ ድጋፍ እንዲያድርግም ምክር ቤቱ ጠይቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.