አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለ2016 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡:
በመልዕክታቸውም÷ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ሞ ያጋጠሟትን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ተቋቁማ
በማህበራዊ ኢኮኖሚ ልማት በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቧን አውስተዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያን በቀጣይ ያሉብንን የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይት እና በመደማመጥ በመፍታት ዘመኑን የዋጀ የሰለጠነ ፖለቲካ ልናራምድ ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታትም ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
የበለጸገችና ሕብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ማስረከብም የእያንዳንዱ ዜጋ ታሪካዊ ሃላፊነት እና ሞራላዊ ግዴታ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ከትናንት ትምህርት በመውሰድ ዛሬን የተሻለ ለማድረግ እና ነገን በመልካም አቅጣጫ ለመጓዝ ሁላችን ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለእርቅ፣ ለመግባባትና ለአንድነት ቁርጠኛ ልንሆን ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡