Fana: At a Speed of Life!

በደመራ በዓል አከባባር የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከደመራ በዓል አከባባር ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳስቧል፡፡

በመስቀል ደመራ በዓል አከባባር ሥነ ሥርዓት ላይ የእምነቱ ተከታዮች በተለያዩ ቦታዎች ችቦ የማብራት ሥነ ሥርዓት ያካሂዳሉ፡፡

በዚህ ወቅትም የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የአገልግሎቱ ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

ደመራ ሲለኮስ ከኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ ትራንስፎርመሮች እና ማስተላለፊያ መስመሮች በበቂ ርቀት መከናወኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ጥንቃቄ ባልተሞላበት ሁኔታ ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ጋር ንክኪ በሚፈጠር መልኩ የማስዋብ ሥራዎች ማከናወንና ችቦ መለኮስ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ዜጎች በበዓላት ወቅትም ሆነ በአዘቦት ቀናት የትኛውም ክንውን በተቻለ መጠን ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በራቀ ሁኔታ ማከናወን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በበዓላት ወቅት የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት የበኩልን ትብብር እንዲያደርግ አቶ አንዋር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዜጎች ከኤሌክትሪክ ጋር በተገናኘ አደጋ ሲያጋጠም ወይም ሌላ መረጃ ሲፈልጉ በተቋሙ የደንበኛ ግንኙነት ማዕከል ስልክ ቁጥሮች 905/904 በመደወል ጥቆማ እንዲሰጡም ጠይቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.