Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል አመራሮች ለተፈናቀሉ ወገኖች ማዕድ አጋሩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የጋምቤላ ክልል አመራሮች ለተፈናቀሉ ወገኖች እና አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርተዋል፡፡

የማዕድ ማጋራቱ በጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ቴንኩዌይ ጆክ እና በክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ባንቻየሁ ድንገታ የተመራ የክልሉ አመራሮች ቡድን የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለተፈናቀሉና አቅም ለሌላቸው ወገኖች የተደረገ ነው።

በማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብሩ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ፥ አዲስ ዓመት ሲከበር አቅመ ደካሞችንና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት በማሰብ ሊሆን ይገባል።

በህዝቦች መካከል የነበረውን የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች በሚያጠናከር መልኩ በዓሉን ማክበር እንደሚገባም አመልክተዋል።

አመራሩ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ተገኝቶ በዓሉን ያከበረበት ዋና ዓላማ ቀደም ሲል በወረዳው ተከስቶ በነበረ የፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉና አቅም የሌላቸው ወገኖችን ማዕድ ለማጋራት በማሰብ መሆኑንም ነው የገለጹት።

አመራሩ በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ ከህዝቡ ጋር ያለውን አብሮነት ለማሳየት ጭምር ታስቦ እንደሆነም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ላክዴር ላክባክ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በአዲሱ ዓመት በክልሉ ሰላምን አጠናክሮ በማስቀጠል ህዝቡን በልማትና በመልካም አስተዳደር ለመካስ በትኩረት ይሰራል።

በተለይም ቀደም ሲል የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በመሆኑም ሁሉም ሰላሙን አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለበት መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.