Fana: At a Speed of Life!

የከምባታ ብሔር ዘመን መለወጫ “የማሳላ” በዓል በመከበር ላይ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከምባታ ብሔር የዘመን መለወጫ የማሳላ በዓል በከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ በመከበር ላይ ይገኛል።

በዓሉ ትናንት የጀመረ ሲሆን በዛሬው እለትም በርካታ ታዳሚ በተገኘበት በከምባታ ሁለገብ ስቴዲየም በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው።

በከምባታ ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የማሳላ በዓል÷ አብሮነት የሚደረጅበት፣ በናፍቆት የሚጠበቅና በከፍተኛ ዝግጅት ደምቆ የሚከበር በዓል ነው።

ማህበረሰቡ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ በማሰብ ለበዓሉ አከባበር የሚረዱ ቁሳቁስ እና ለባህላዊ ምግቦች ዝግጅት የሚሆኑ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራ ከወራት በፊት ያከናውናል።

እናቶች የቅመማ ቅመሞችና ለባህላዊ ምግብ (አታካና) ዝግጅት የሚሆን ቆጮ ማሰናዳት እንዲሁም ለበዓል የሚሆን ቂቤን በስፋት የማጠራቀሙ ተግባር ለወራት ይከናወናል።

የበሬ መግዛትና አርዶ በዓልን ከጎረቤት ጋር በጋራ ለማሳለፍም አባቶች ቀደም ብለው ለበሬ ግዢው ገንዘብ በማጠራቀምና በማስቀመጥ ለበዓል የሚሆን ሰንጋ የሚሸምቱበት ልዩ ጊዜ አላቸው።

የብሔሩ ተወላጆች በማሳላ በዓል በግጭት ውስጥ ሆኖ አዲስ ዓመትን መቀላቀል የለባቸውም ተብሎ ስለሚታመን በሀገር ሽማግሌዎች የተጣሉትን የማስታረቅ ሥርዓትም ይከናወናል።

ከችቦ ዝግጅት ጀምሮ የደመራ ማብራት ሥነ ስርዓትና ሌሎች ባህላዊ መስተጋብሮች በአብሮነት የሚከወኑ እሴቶች ናቸው።

የማሳላ በዓል ዛሬ በአደባባይ በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች ታጅቦ እየተከበረ የሚገኝ ሲሆን÷ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት የማሳላ ታላቁ ሩጫም ተካሂዷል።

በዚህ የማሳላ ሳምንት ተብሎ በተሰየመው የበዓል አከባበር በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎችም መሰል ዝግጅቶች እየተከናወኑ የሚቀጥሉ ይሆናል።

የመስከረም ወር በከምባታ በደስታና በፍቅር የሚታለፍ ወር ሲሆን÷ከተለያዩ አካባቢዎች ለበዓል ወደ ቤተሰቦቻቸው የመጡ የብሔሩ ተወላጆችም ወቅቱን በበዓል ድባብ ውስጥ ሆነው ከቤተሰቦቻቸው እና አካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን በደስታ ያሳልፋሉ።

በብርሃኑ በጋሻው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.