ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች 10 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
የትምህርት ቢሮው መርሐ-ግብሩን ያሰናዳው “ተደራሽና አካታች ፍትኀዊ የትምህርት አገልግሎት ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች” በሚል መሪ ቃል ነው፡፡
ድጋፉ በከተማዋ አሥተዳደር ትምህርት ቢሮ ሥር ለሚገኙ 18 የድጋፍ መስጫ ማዕከላት የተከፋፈለ ነው።
ቢሮው 28 የድጋፍ ዓይነቶችን ያማከለ ሲሆን በድጋፉ ዓይነ ስውራን ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ተመላክቷል።
ድጋፉ ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ለሚገኙ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች መሆኑም ተገልጿል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች÷ ከዚህ ቀደም አጋዥ የትምህርት ቁሳቁስ ባለማግኘታቸው አጥጋቢ ውጤት እንዳያስመዘግቡ እክል ሆኖባቸው እንደነበር አስታውሰው፤ ድጋፉ ችግሩን እንደሚቀርፍላቸው ተናግረዋል።
የልዩ ፍላጎት ትምህርት የራሱ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ለማድረግ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በታሪኩ ወልደ ሠንበት