አፍጋኒስታን ለሁለተኛ ጊዜ በከባድ ርዕደ መሬት ተመታች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍጋኒስታን በቀናት ልዩነት በከባድ ርዕደ መሬት ለሁለተኛ ጊዜ መመታቷ ተሰምቷል፡፡
በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 3 የተመዘገበ ከባድ ርዕደ መሬት በሄራት ግዛት ከተከሰተና ከ 2 ሺህ 400 በላይ ሰዎችን ለህልፈት ከዳረገ ከቀናት በኋላ ነው ለሁለተኛ ጊዜ ተመሳሳይ አደጋው የተከሰተው።
አደጋው የሄራት ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በሄራት አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ ዛሬ ማለዳ ላይ እንደተከሰተ ተገልጿል።
የአካባቢው አስተዳደር ጽ/ቤት ቀደም ሲል በተከሰተው ርዕደ መሬት በፈራረሱ አካባቢዎች ትልቅ ኪሳራ እንደደረሰ ገልጿል፡፡
ይሁንና በትንሹ 80 ሰዎች መቁሰላቸውን እና አደጋውን ተከትሎ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ዋናው የሄራት ጎዳና መዘጋቱን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አብዱልዋሂድ ራያን ተናግረዋል።
የታሊባን ባለስልጣናት እንደተናገሩት፤ በዓመቱ በተከሰተ ከባድ ርዕደ መሬት አደጋ ቢያንስ 2 ሺህ 445 ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል።
የነፍስ አድን ሰራተኞችና በጎ ፈቃደኞች ከሳምንቱ መጨረሻ ጀምሮ በመንደሮች የተረፉትን እና አስከሬኖችን ከፍርስራሽ ሥር ለማውጣት ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነ የአልጀዚራ ዘገባ ያመላክታል።