Fana: At a Speed of Life!

የቀድሞ ተዋጊዎች ጦርነቱ ያስከተለውን ጉዳት በመረዳት ሰላምን ለማጽናት ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ ተዋጊዎች ያለፈው ጦርነት ያስከተለውን ጉዳት በመረዳት የሀገርን ሰላም ለማፅናት ግንባር ቀደም ሆነው መገኘት እንዳለባቸው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ።

አምባሳደር ተሾመ ÷ በግጭት ውስጥ የቆዩ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋምና ዘላቂ ሰላም መፍጠር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በ2016 ዓ.ም የሰላም ሒደቶችን ዘላቂ ለማድረግ ትኩረት መስጠቱ ተገቢና ሁሉም ለተግባራዊነቱ ሊደግፈው የሚገባ መሆኑንም ተናግረዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስና በልማት ለማሳተፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ ለስኬቱ የሰላም ጥረቶችን ማገዝና በጋራ መስራትም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በግጭቶች ውስጥ የተሳተፉ አካላትም በመነጋገር በሰላማዊ ውይይት ችግሮችን ለመፍታት ሊዘጋጁ ይገባል ነው ያሉት።

“ጦርነት ሁሉንም የሚጎዳውን ያህል ሰላም ሁሉንም ይጠቅማል” ያሉት ኮሚሽነሩ÷ የመንግስት የሰላም ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሁሉም እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችም በጦርነቱ ወቅት በራሳቸው፣ በቤተሰባቸውና በአካባቢያቸው የደረሰውን ጉዳት በመገንዘብ የሰላም አርዓያ ሆነው ሊንቀሳቀሱ ይገባል ነው ያሉት።

በሃይል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ትጥቅ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላትም ቆም በለው በማሰብ በውይይት ችግሮችን ለመፍታት ሊዘጋጁ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.