Fana: At a Speed of Life!

ተቋማት በሳይበር ምህዳር ያላቸው የሰው ሃይልና የቴክኖሎጂ አቅም 20 በመቶ በታች መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2016፣ (ኤፍ ቢ ሲ) ተቋማት በሳይበር ምህዳር ያላቸው የሰው ሃይል ብቃት፤ የቴክኖሎጂ አቅም እና የተቋማዊ አደረጃጀት ዘርፉ ከሚፈልገው ከ20 በመቶ በታች መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ፡፡

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ÷ የሳይበር ጥቃት ከየትና መቼ፣ በምን ሁኔታ እንደሚፈጠር የማይታወቅ ውስብስብና ዓይነት ብዙ የደህንነት ስጋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም ከተሰነዘረ 214 የሳይበር ጥቃት አይነቱና መጠኑ ጨምሮ በ2014 ዓ.ም ወደ 8 ሺህ 845 ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡

ተቋማት በሳይበር ምህዳር ያላቸው የሰው ሃይል ብቃት፣ የቴክኖሎጂ አቅም እና የተቋማዊ አደረጃጀት ዘርፉ ከሚፈልገው ከ20 በመቶ በታች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የነገው ትውልድ የሀገር ሉዓላዊነትና ደህንነት ማስጠበቂያ ተቋም መሆኑን ገልጸው፥ ተቋማት በሳይበር ምህዳር ላይ ያላቸውን የሰው ሃይልና የቴክኖሎጂ አቅም ማዳበር አለባቸው ብለዋል፡፡

የሀገሪቱን የሳይበር ሃይል ለማሳደግ ውስጣዊ አቅምን ከማጎልበት ባሻገር በሀገራዊው የሳይበር ታለንት ማዕከል አማካኝነት ወጣቶችን በማሰልጠንና በማብቃት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የክረምት መርሐ ግብር ከ1 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች መካከል 62 ወጣቶች የተለያዩ ደረጃዎችን አልፈው ከ26 በላይ ቴክኖሎጂዎችን አልምተዋል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ወጣቶቹ በጋራ በመሆን ሥራ ላይ መዋል የሚችሉ 14 ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ላይ ሲሆኑ÷ ቀሪዎቹ ደግሞ የአስተዳደሩ የሳይበር ወታደር ሆነው እያገለግሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮው የ2016 በጀት ዓመት በሀገራዊ የሳይበር ታለንት ማዕከል ለክረምት ትምህርት 5 ሺህ 600 ወጣቶች ማመለክታቸውንም ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.