Fana: At a Speed of Life!

ብሪክስ-ገዝ የበይነ መረብ አገልግሎት ሊኖር እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ አባል ሀገራት የራሳቸው የበይነ መረብ አገልግሎት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

የሩሲያው ዱማ መቆጣጠሪያ ኮሚቴ የመጀመሪያ ምክትል ሊቀመንበር እና የሩሲያ የሕግ ባለሙያ ዲሚትሪ ጉሴቭ፥ የራስ ገዝ በይነ- መረብ መኖር የአባል ሀገራቱን ባህላዊ እሴቶች ለመጠበቅ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

ዲሚትሪ ጉሴቭ ፥ ሩሲያ ከሌሎች የብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በመሆን ተለዋጭ የበይነ መረብ አገልግሎት ማዘጋጀት እንዳለባት ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

በዚህም ፥ “የብሪክስ የሳይበር ምህዳር” ለመፍጠር እንዲሰራ ለሩሲያ የዲጂታል ልማት፣ ኮሙኒኬሽን እና የመገናኛ ብዙሃን ሚኒስቴር ኃላፊ ለማክሱት ሻዳየቭ ጥያቄ ቀርቧል ነው የተባለው፡፡

“ባህላዊ እሴቶች እና መልካምነት የሰፈነበት በይነ መረብ” ለማዘጋጀት የቀረበው ሃሳብ “የአጠቃላይ የብሪክስን ቴክኒካዊ፣ ድርጅታዊ እና ሥልጣኔን በመጠቀም” ተግባራዊ እንደሚሆን ተነስቷል፡፡

እንደ ጉሴቭ ገለጻ ፥ በአሁኑ ወቅት በሩሲያ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ እየተካሄደ ያለው 5ኛው ዓለም አቀፍ የማዘጋጃ ቤት ፎረም የብሪክስ አባል ሀገራት አንድ ወጥ የሆነ የበይነ መረብ አገልግሎትን አስመልክተው ውይይት ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ነው።

ሩሲያ፣ ብራዚል፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካን አካትቶ የነበረው ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቅርቡ የተቀላቀሉትን አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶችን አባል በማድረግ መስፋፋቱ ይታወቃል፡፡

ይህ ቡድን በፈረንጆቹ 2040 ከዓለም አቀፉ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ ግማሽ ያህሉን እንደሚይዝ መተንበዩን አርቲ በዘገባውአስፍሯል፡፡

በዚህ ሣምንት መጀመሪያ ላይ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የሁሉንም ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ በዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አገልግሎት ላይ ለውጦች እንዲደረጉ ጠይቀዋል።

በፈረንጆቹ 2023 የዓለም የበይነ-መረብ ኮንፈረንስ የውዝሄን ጉባዔ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ፥ ለልማት ቅድሚያ እንዲሰጥ እና የበለጠ ሁሉን አቀፍ እና የበለጸገ የሳይበር ምህዳር እንዲገነባ እንመክራለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.