Fana: At a Speed of Life!

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ቫይረስ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተስፋፋውን የኢቦላ ቫይረስ ስርጭት ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት የመከላከያ ክትባት ዘመቻ በይፋ አስጀምሯል፡፡

የኢቦላ ቫይረስ ከሦስት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተ ሲሆን÷ በመስከረም ወር መጀመሪያ የቫይረሱ ስርጭት በአስጊ ደረጃ መስፋፋቱ ተመላክቷል፡፡

የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር በቫይረሱ እስካሁን 32 ሰዎች መያዛቸውንና 16 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የክትባት ፕሮግራም ማናጀር ፓትሪክ ኦቲም ቫይረሱ ከተከሰተበት ካሳይ ግዛት አንስቶ በተለያዩ ቦታዎች እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸው÷ እንደ አንጎላ ባሉ ጎረቤት ሀገራትም ሊስፋፋ እንደሚችል ስጋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ተከትሎም የዓለም ጤና ድርጅት የጤና ባለሙያዎችን እና በርካታ መድኃኒቶችን ወደ ኪኒሻሳ በመላክ በዛሬው ዕለት የኢቦላ ቫይረስ የመከላከያ ክትባት ዘመቻን ማስጀመሩ ተጠቁሟል፡፡

የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የመከላከያ ክትባቱ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል።

እስካሁንም ድርጀቱ 400 ዶዝ ኢርቬቦ የተሰኘ የኢቦላ ክትባት ቡላፔ ወደ ተባለችው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከተማ እንዲሁም ከ2 ሺህ ዶዝ በላይ የመከላከያ ክትባት ወደ ብሔራዊ የክትባት ማዕከል ማጓጓዙን አስታውቋል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የክትባት አስተባባሪ ቡድን በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ 45 ሺህ ዶዝ የኢቦላ ቫይረስ መከላከያ ክትባቶችን ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለማጓጓዝ ስምምነት ላይ ተደርሷል ማለቱን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.