ደቡብ ኮሪያ በኒውክሌር ሃይል ልማት ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ኮሪያ በኒውክሌር ኢነርጂ ልማት ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከልንና ብሔራዊ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባትና የኒውክሌር መሠረተ ልማት ለማልማት እየሰራች መሆኑ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ኤምባሲም ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂን ለሰላማዊ መስክ ለመጠቀም የምታደርገው ጉዞ የተሳካ እንዲሆን ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢኖቬሽን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
የአዲስ አበባና አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች ዘርፉ በኢትዮጵያ አዲስ በመሆኑ የሰው ሃይል ማፍራት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ልማት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የማልማት ሥራ ላይ ካደጉ ሀገራት ጋር በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሴኪዮሄ÷ ሀገራቸው በኒውክሌር ሃይል ልማት ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግና በትብብር እንደምትሰራ አረጋግጠዋል፡፡
በተለይም በሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በግብዓት አቅርቦት እና ሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች ላይ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
ደቡብ ኮሪያ በኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ልማት ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ