ከሱዳን ለሚመጡ ፍልሰተኞች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው አለ የምዕራብ ጎንደር ዞን
አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሱዳን የጦርነት ቀጠና ሸሽተው የሚመጡ ፍልሰተኞችን በአግባቡ በመቀበል አስፈላጊውን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታውቋል፡፡
የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ሃላፊ አበባው በዛብህ÷ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ እስካሁን የ75 ሀገራት ዜጎች የሆኑ 88 ሺህ በላይ ፍልሰተኞች በመተማ በኩል ወደ ዞኑ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከስደተኞቹ መካከል ሰነድ የያዙ እና ሙሉ ሰነድ የሌላቸው እንደሚገኙም ሃላፊው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ከፌዴራል መንግስት አካላት እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጋር አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ደግሞ ወደየ አካባቢያቸው ለመሸኘት የትራንስፖርት አገልግሎት ከማቅረብ ጀምሮ ሌሎች ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ምዕራብ ጎንደር ዞን የኢትዮጵያና ሱዳን መዋሰኛ እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊው የፀጥታ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በሰሎሞን ይታየው