Fana: At a Speed of Life!

በአሉታዊ ትርክት ሀገር አይገነባም – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሉታዊ እና በአንድ ሰፈር ትርክት ሀገር እንደማይገነባ ማመን እና አብሮነትና አቃፊነትን መቀበል ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ሲሆን፥ “ችግሮቻችንን እኩል የምንረዳው ከሆነ ጉዟችን ወደ መፍትሄ ይሆናል በችግሮች ላይ የማንግባባ ከሆነ ግን ውጤታማ መሆን ያስቸግራል” ብለዋል፡፡

አሁን በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የችግር ትንታኔ ስሜት ይጫነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ የማያግባባና ከእውነት እንድንርቅ የሚያደርገን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

አያይዘውም “ላሉን ችግሮች የሴራ ትንታኔ ይበዛዋል፤ይህም ከእውነት ያርቀናል የተስተካካለ መፍትሄ ለማምጣት ይቸግራልም” ነው ያሉት፡፡

በብልፅግና የሚመራውን መንግስት በሚመለከት ባለፉት 5 ዓመታት ወቀሳ እና ክሶች እንሰማለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ብልፅግና ሸኔ ነው፣ ዘውዳዊ ነው፣ ደርግ ነው ይላሉ ብልፅግና በአንድ ጊዜ ሶስቱን መሆን አይችልም፤ ይህ የሚያሳየው ስሜት እና ሴራ የበዛበት መሆኑን ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ የዳቦ ስሞች እኛን አይገልፁንም፤ እኛ የትኛውም ሰፈር ፅንፍ የወጣ ዋልታ የረገጠ አስተሳሰብ መጠቀሚያ አንሆንም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው፡፡

እኛ እንደ ፓርቲ ሃገራዊ እይታ ነው ያለን ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ በሁሉም ጫፍ ያሉ ዜጎቿ እኩል በነፃነት የሚኖሩባት፤ የጎላች፤ ያማረች፤ የበለፀገች ሃገር የምትፈጠርበት መንገድ እናያለን ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የእያንዳንዱ ዜጋ ውጤት ናት፤ በጋራ መኖርና በጋራ መበልጸግም እንችላለን የሚል እምነት ነው ያለን ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ችግሮች ለእኛ አዲስ አይደሉም ፤ ችግር የሆነው ያንን ቀይሮ አምርቶ መብላት ነው ሲሉም አንስተዋል።

ሰላም መሆን፤ ለዚህም መትጋትን፣ መነጋገርን እናስቀድም እና ከዚህ ታሪካችን እንውጣ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በአሉታዊ እና በአንድ ሰፈር ትርክት ሀገር እንደማይገነባ ማመን እና አብሮነትንም አቃፊነትም መቀበል ያስፈልጋል የሚል እምነት አለንም ብለዋል፡፡

ስንለያይ እንጎዳለን የሚያሰባስበን ነገር እናምጣ ሲሉም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.