በአቶ አሻድሊና አቶ ጥላሁን የተመራ ልዑክ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎበኘ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የተመራ ልዑክ በአሶሳ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በአሶሳ ከተማና ዙሪያው በሌማት ትሩፋት አካል የሆኑ የዶሮ እርባታ ፣ የእንስሳት እርባታ እና ሌሎች እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን ነው ተዘዋውረው የተመለከቱት።
አቶ አሻድሊ ሀሰን የማህበረሰብ አቀፍ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የስርዓተ ምግብ ምጣኔን ማስተካከል ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በቅርቡ ወደ ስራ የገባው የሌማት ትሩፋት በክልሉ በስፋት እየተተገበረ እንደሚገኝና አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ተስፋ ሰጭ የልማት እንቅስቃሴዎች እንደተመለከቱ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ክልሉ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አቅም የሚሆኑ ገጸ-በረከቶች ያሉት ክልል እንደመሆኑ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አንስተዋል፡፡