Fana: At a Speed of Life!

በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ 812 ሚሊየን ብር ገደማ ከምዝበራ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በተከናወነ አስቸኳይ ሙስና የመከላከል ሥራ 812 ሚሊየን ብር ገደማ ከምዝበራ ማዳን መቻሉን ገለጸ፡፡
ኮሚሽኑ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድና የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡
ዋና ኮሚሽነር ሳሙኤል ሁርቃቶ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ አጠቃላይ የፀረ ሙስና ሀገራዊ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውን ታሳቢ በማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ የትውልድን ስነ-ምግባር በተገቢው በመገንባት በ2022 ከሙስና የፀዳች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ዓላማ ይዞ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በ2014/15 ሙስናን በመከላከል ረገድ የተጠኑ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ በሁሉም ዘርፎች ላይ የተደራጀ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡
በዚህም ነፃና ገለልተኛ በሆኑ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ጥናት መካሄዱን ያነሱት ኮሚሽነሩ÷ ጥናቱ በየዘርፎቹ ያሉትን የሙስና ስጋቶች በግልፅ ያሳየ መሆኑን እና ያንንም ለባለድርሻ አካላት ማቅረብ መቻሉን አመላክተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለማሳካት ከያዛቸው ግቦች አኳያም ለዜጎች ግንዛቤ መፍጠር የሚችሉ 5 የተመረጡ ሰነዶችን በማዘጋጀት በተሰራ ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 41 በሚሆኑ በዘርፍ ደረጃ በተከናወኑ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ተግባራት ወደ 672 ሚሊየን ብር ማዳን መቻሉን ለማሳያነት አቅርበዋል፡፡
በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በተከናወኑ 51 የሚሆኑ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራዎችም 139 ሚሊየን ብር ያህል ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም በአጠቃላይ 92 በሚሆኑ ጥቆማዎች ላይ ጥናት ተሰርቶ 812 ሚሊየን ብር ያህል ከምዝበራ ማዳን መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ይህም የኮሚሽኑ ፀረ ሙስና መከታተያ ክፍል ወንጀሉ ከመከሰቱ በፊት በደረሱት ጥቆማዎች መሠረት እንዲቋረጡ በማድረግ የመንግስትን ሀብት ማዳን የተቻለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽኑ አሰራሩን በማዘመንም ከክልሎች ጋር ትስስር ፈጥሮ መስራት የሚያስችለውን የዲጂታል አሰራር ስርዓት መዘርጋቱንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
በታምራት ቢሻው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.