ልማት ባንክ የግብርና ዘርፉን በስፋት ለመደገፍ የሚያስችል የወለድ ተመን ማሻሻያ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የግብርና ዘርፉን በስፋት ለመደገፍ የሚያስችል የወለድ ተመን ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ÷ በግብርና ዘርፍ በአነስተኛ፣ መካከለኛና የኮርፖሬት ፕሮጀክት ብድር 11 ነጥብ 5 በመቶ የማበደሪያ የወለድ ተመን ወደ 7 በመቶ ዝቅ መድረጉን ገልጿል፡፡
ማሻሻያው ባንኩ በሊዝ ፋይናንስ እና በፕሮጀክት ፋይናንስ የብድር ሞዳሊቲ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የማሻሻያው ዓላማ የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ማሳካት እንዲቻልና የግብርና ሴክተሩን በማነቃቃት በዘርፉ የግል ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እና ለመሳብ ነው ተብሏል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የወለድ ተመን ማሻሻያው ወቅቱን የጠበቀና በኢትዮጵያ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማዕከል ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ የሆነ ያልታረሰ የመሬት ሃብት ወደ ስራ ለማስገባት፣ ባለሃብቶች፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የበለጠ እንዲበረታቱ ለማድረግ የወለድ ተመን ማሻሻያ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡
ማሻሻያው ዘርፉን ለማሳደግ የታቀደው ስትራቴጅያዊ ሪፎርም አካል ሲሆን÷ መንግስት የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራ ያለውን ስራ የበለጠ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።