ችግር የምንፈታበት መንገድ ጥራኝ ዱሩ በሚል ስሜት መሆን የለበትም – አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ችግር የሚፈታበት መንገድ በእልህ እና በየጊዜው ጥራኝ ዱሩ በሚል ስሜት ሳይሆን በሰከነ እና በበሰል መንገድ ሊሆን ይገባል አሉ የታሪክ፣ ቅርስ እና ባህል ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር)፡፡
ተመራማሪው ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥ ታሪክን ማወቅ ትናንት የተከሰቱ ችግሮች የተፈቱበትን መንገድ ለማወቅ እና ታሪካዊ ሂደቶችን ለመረዳት ያስችላል፡፡
ታሪክን መረዳት አስተሳሰብን የበለጠ እንደሚያጎለብት ጠቁመው፤ በዚህ ሂደት የተገኘ እና ጊዜው የሰጠንን እውቀት በመጠቀም ችግሮችን መፍታት መቻል አለብን ብለዋል፡፡
ሀገር እና ስርዓት የተለያዩ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሀገር ቋሚ ናት፤ ስርዓት ይለዋወጣል ያሉት ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር)፤ የፖለቲካ ሂደታችንን በዚህ መልኩ መቃኘት እና ማስተካከል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ካጠናከሩ የውጭ ጫና መቋቋም እንደማይከብዳቸው አመልክተዋል፡፡
ከጥንት ጀምሮ የስልጣኔ አካል የሆነችው ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ የስልጣኔዎች መራኮቻም እንደሆነች ገልጸዋል፡፡
በብርሃኑ አበራ