በዳሰነች ወረዳ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 23 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደና ሌሎች ከፍተኛ አመራር አባላት በወረዳው በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችን የተመለከቱ ሲሆን÷ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልበት ዙሪያ ከተጎጂዎች ጋር ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ÷ የኦሞ ወንዝ ያስከተለውን ከፍተኛ ጉዳት በዘላቂነት ለመፍታት በክልሉ የተቋቋመው የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚቴ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ የሰብአዊ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ አርብቶ አደሮች የምግብ ዱቄት፣ አልባሳትና ምግብ ማብሰያ ቁሳቁስ ለአርብቶ አደሮቹ ድጋፍ አደርገዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ዜጎች የክልሉ መንግስት አመራር አባላት የገጠማቸውን ችግር ለመመልከት በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።