ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ተቃርባለች -ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ተቃርባለች አሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፡፡
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር የደረሰበትን ሂደት አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በስዊዘርላንድ ጀኔቫ የተካሄደው 6ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የስራ ቡድን ስብሰባ ስኬታማ እና የአባል ሃገራትን ቀልብ የሳበ መሆኑን አንስተዋል።
በመድረኩ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን ከ30 በላይ ሃገራት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው÷6ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ ከሌሎች ሃገራት ልምድና ክህሎት የተገኘበት እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ይሄም ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለድርጅቱ አባልነት መቃረቧን የሚያመለክት ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷በቀጣይም ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ይሰራልም ነው ያሉት።
ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር ለማድረግ ፍላጎት ካላቸው አባል ሃገራት ከ200 በላይ መቅረባቸውን እና በቀጣይም የድርድር ሂደቱን አጠናክሮ በመቀጠል የባለብዙ ወገንና የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድሮች የሚከናወኑ ይሆናልም ብለዋል።
7ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ በመጪው ጥር 2018 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑንም አስታውሰዋል።
በየሻምበል ምህረት