የአማራ ክልል ለታጣቂ ሃይሎች የሰላም ጥሪ አስተላለፈ
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለታጠቁ ኃይሎች በሰባት ቀናት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመንግስት በመስጠት ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ ጥሪ አቀረበ።
የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፋንታው (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ወራት የታጠቁ ሃይሎች የጸጥታ ችግር በመፍጠር በክልሉ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሰዋል።
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በመከላከያ ሰራዊት እና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በጋራ ባደረጉት ተጋድሎ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸዋል።
በተደረገው ትግልም ታጣቂ ሃይሉ በመንግስትና ህዝብ ላይ ለማድረስ ያቀደው የጥፋት ሴራ አሁን ላይ እየከሸፈ መምጣቱን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ጋር በመነጋገር ተጨማሪ የደም መፋሰስን ለማስቀረትና ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት እንዲቻል የሰላም እድል እንዲፈጠር ወስኗል።
በዚህም በህገወጥ መንገድ የታጠቁ ኃይሎች በየአካባቢያቸው ለሚገኙ የኮማንድ ፖስት ማስተባበሪያዎችና ለሀገር ሽማግሌዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ውሳኔ መተላለፉን አስረድተዋል።
የዞንና የወረዳ አመራሮችም በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን የሚሰጡ ታጣቂ ኃይሎችን በሰላም መቀበል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የሚገቡ ኃይሎችም እስካሁን በፈጸሙት ወንጀል የማይጠየቁ ሲሆን አስፈላጊውን የተሀድሶ ስልጠና በመውሰድ ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ አስፈላጊው ትብብር ይደረጋል ብለዋል።
መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ አልቀበልም ብለው በህገወጥ ድርጊታቸው በሚቀጥሉት አካላት ላይ የተጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።