Fana: At a Speed of Life!

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገንባት በተፋሰሱ ሀገራት ጉዳት እንደማያደርስ ግብፅ ታውቃለች- ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት በግብፅም ሆነ በተፋሰሱ ሀገራት ጉዳት እንደማያደርስ ግብፅ ታውቃለች ሲሉ ምሁራን ተናገሩ፡፡
 
ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ግብጽ የቀድሞው የቅኝ ግዛት ውል ተፈጻሚ እንዲሆን በመሻቷ ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
 
ይህን ተከትሎም በጉዳዩ ላይ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የታሪክና የዲፕሎማሲ ምሁራን ግብጽ ዛሬም የቅኝ ግዛት ውልን ዋና መደራደሪያ አድርጋ ማቅረቧ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ግብፅ በየድርድሩ መከራከሪያ አድርጋ የምታቀርበው “የቅኝ ግዛት ውል” ኢትዮጵያ በታሪኳ ተግብራው የማታውቅ፣ ጊዜውንም የማይመጥን እና በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሐሳብ መሆኑን በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር አህመድ አሊ ተናግረዋል፡፡
 
በሁሉም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድሮች ግብጽ የምታነሳው አግላዩ የቅኝ ግዛት ውል የሀገሪቱ መንግስት የዜጎችን ልብ ለመግዛት የሚጠቀምበት አቋም መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
 
በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም በበኩላቸው÷ ግብፅ የምታቀነቅነው የቅኝ ግዛት ውል ኢትዮጵያን ያገለለና በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
ግብጽ ዛሬም አግላይ የሆነው የቅኝ ግዛት ውል ተፈጻሚ እንዲሆን ከያዘችው አቋም መለሳለስ አለማሳየቷም ከጥንት ጀምሮ የዓባይን ወንዝ በበላይነት ለመቆጣጠር ስታራምደው ከነበረው እሳቤ ለውጥ አለማምጣቷን ያሳየል ነው ያሉት፡፡
 
ይህ ደግሞ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የማታምን መሆኗን ያስረዳል ብለዋል፡፡
 
የታላቁ ህዳሴ ግድብ በግብፅም ሆነ በተፋሰሱ ሀገራት ጉዳት እንደማያደርስ ግብፅ ታውቃለች ያሉት ምሁራኑ÷ ስምምነት ላይ እንዳይደረስ እንቅፋት የምትፈጥረው በኢትዮጵያ የወደፊት የመልማት ጉዞ ላይ ጫና ለማሳደር በመሻት ነው ብለዋል።
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ከጅምሩ “በጋራ እንጠቀም” የሚል መርህ ይዛ የቀረበችው ኢትዮጵያ በቀጣይም ለድርድር በሯን ሳትዘጋ በያዘችው አቋም መቀጠል ይኖርባታል ሲሉም መክረዋል፡፡
 
በተስፋዬ መሬሳ
 
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.