የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተጠናቅቋል፡፡
ሥልጠናው የላቀ የሕዝብ አመኔታና እርካታ ለመፍጠር እንዲሁም እርስ በርሱ የሚናበብ ቀልጣፋ የአገልግሎት ሥርዓት ያለው ተቋም ለመገንባት ግብዓት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
አመራሩን ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ ጉዳዮችን ከሀገራዊውና ከከተማዋ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በመተንተን መረዳትና የአስተሳሰብ አድማሱን ለማሥፋት የንድፈ ሐሳብና የተግባር ሥልጠና መውሰዱም ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከከተማዋ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበትና የፐብሊክ ሰርቪስ ለሕዝብ እርካታና ለመንግስት አመኔታ ያለውን ፋይዳ በሥልጠናው በትኩረት መሠጠቱ ተነግሯል፡፡
በሥልጠናው ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷ “ሥልጣናው በምርጫ ከሕዝብ የተቀበልነውን አደራና አመኔታ ወደ ተጨባጭ ተሥፋ መቀየር የሚያስችል አቅም መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ”ብለዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኘውን አመራርና ፈጻሚ እያበቃን ሕዝቡን በቅንነት በታማኝነት እንዲያገለግል እናደርጋለን ማለታቸውንም የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡