Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው አሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፡፡

ለተከታታይ ሦስት ቀናት በልዩ ልዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲካሄድ የቆየው የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል።

ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የምክር ቤቱን ስብሰባ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በየአመቱ መሻሻል በማሳየት ወደ ሁለት አሃዝ እየተንደረደር ይገኛል፡፡

ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ላይ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፥ በዚህም ኢትዮጵያ ጠንካራና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው ብለዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የዜጎችን ኑሮና የአመጋገብ ሁኔታ ከማሻሻል ባለፈ ለበርካቶች የስራ እድል መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡

የማዕድን ዘርፍ የኢኮኖሚያችን ምሶሶ ሆኗል ያሉት ሚኒስትሯ፥ የማዕድን ሀብታችንን በአግባቡ በመለየት የአካባቢውን ማህበረሰብ በሚጠቅም መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ቱሪዝም ላይ በተሰራ ስራ ኢትዮጵያን የኮንፈረንስ ማዕከል ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፥ በዓመት ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በማስተናገድ ኢትዮጵያ መስራት እንደምትችል አሳይታለች ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ በከተማ ልማት፣ በጤና እና በትምህርት ዘርፎች እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስገንዝበዋል፡፡

የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና የሀገርን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ መደረጋቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.