ሰብዓዊ መብት የምናከብረውና የምናስከብረው ለማንም ብለን ሳይሆን ለህዝባችንና ለፍትህ ስንል ነው- ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ሰብዓዊ መብት የምናከብረውና የምናስከብረው ለማንም ብለን ሳይሆን ለህዝባችን እና ለፍትህ ስንል ነው” ሲሉ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ሰሞኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት ዙሪያ በፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት፥ “በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣውን መግለጫ ተመልክተነዋል” ያሉት ወይዘሮ አዳነች፥ ሪፖርቱን የማጣራት ስራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
“የማጣራት ስራችንን አጠናቀን ምላሽ ለመስጠት በሂደት ላይ እያለን መግለጫው በተለያዩ ሚዲያ ተሰራጭቷል” ሲሉም ጠቅሰዋል።
“አሁንም ቢሆን ዘገባውን ከይዘቱ፣ ከአካሄዱ፣ እንዲሁም የጉዳዩን እውነተኛነት እና ገለልተኛነት የማጣራት ስራችንን በቶሎ ለማጠናቀቅ እየሰራን ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
“በማጣራት ስራችን በሚገኘውም ውጤት፣ ሪፖርቱ እውነት በሆነበት ልክ፣ መወሰድ ያለበቸውን እርምጃዎች እንወስዳለን” ብለዋል ወይዘሮ አዳነች በመልእክታቸው።
ሀሰት በሆነበት ወይም በተጋነነበት አኳያ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋራ በመወያየት ሪፖርቱ እንዲስተካከል ለማድረግ እንደሚጥሩ በመግለፅ፤ “ይህ ባይቻል እንኳን ህዝቡ እና አለም ዓአፉ ማህበረሰብ እውነቱን እንዲያውቀው በመረጃ አስደግፈን እናሳያለን” ሲሉም አስታውቀዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።