Fana: At a Speed of Life!

ዘረኝነትና ጎጠኝነት የተስፋፋው እውነት መስፈሪያዋ በመቅጠኑ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሁኑ ዘመን ዘረኝነት፣ ጎጠኝነትና ጽንፈኝነት የተስፋፋው የእውነት መስፈሪያዋ በመቅጠኑ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ30 ዓመታት ያህል ተቋርጦ የቆየውንና በዘመናዊ መልክ የተገነባውን የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ በዛሬው ዕለት መርቀው በይፋ ሥራ አስጀምረዋል።

ደብረ ማርቆስ በወሎ እና ወለጋ መካከል ድልድይ ሆና ንግድንና ሰውን አስተሳስራ እድገትን ስታሳልጥ የኖረች ከተማ እንደነበረች ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከ70 ዓመታት ገደማ በፊት በኢትዮጵያ ካሉ 20 የተሻሉ ከተሞች ተወዳድራ አንደኛ እንደነበረች አስታውሰዋል፡፡

ይህን ሀቅ ማስቀጥል አቅቶን በአባይ ሸለቆ አሊ ዶሮ አካባቢ የሸፈተውንና ወደ አዲስ አበባ አላሻግር ያለውን ሽፍታ በጋራ ታግለን ማስቀረት ሲገባን ወደ ደጀን መሄድ እንዳንችል ተጨማሪ ሽፍቶች ማበራከታችን ተገቢ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡

የትም ቦታ ያሉ ሽፍታዎችን ተሰናስለንና ተደምረን በማስወገድ የህዝባችንን ሰላምና ልማት ማረጋጋጥ ይገባናል ነው ያሉት፡፡

በዚህ ዘመን እውነት መስፈሪያዋ በእጀጉ የቀጠነ በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘረኝነት፣ ጽንፈኝነት እና ጎጠኝነት እንዲስፋፋ አንዱ ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ወደ ቀያችን ሽፍቶች እየተበራከቱ ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሰው ስራ ወደማይሰሩበት ደረጃ ደርሰዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ አጠያያቂና ልንማርበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ተዋድደንና ተከባበረን መኖር የምንችልበት ያማረ ሀገር እንዳለን ጠቁመው፥ ባንግባባ እንኳን ተወያይተንና ተከራክረን ሳንገዳደል አብሮ መኖር ይገባናል ሲሉ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በትዕግስት ግዛቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.