Fana: At a Speed of Life!

በዓዲግራት ከተማ በ651 ሚሊየን ብር የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ651 ሚሊየን ብር የ12 የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ከጥር ወር ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን የዓዲግራት ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

የግንባታዎቹ ወጪ የከተማ አሥተዳደሩ በመደበው 351 ሚሊየን እና የዓለም ባንክ ባደረገው የ300 ሚሊየን ብር ድጋፍ የሚሸፈን ነው፡፡

ግንባታቸው በመካሄድ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል የሁለት ኪሎ ሜትር የአስፋልት ማንጠፍ ሥራ፣ 8 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ኮብል ስቶንና ጠጠር የማልበስ ሥራ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል የሰባት ኪሎ ሜትር ማፋሰሻና 270 ሜትር ርዝመት ያለው የእግረኞችና የተሽከርካሪዎች መሸጋገርያ ድልድይ ግንባታም መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የ17 ኪሎ ሜትር የውኃ መስመር ቁፋሮና የቱቦ ቀበራ እንዲሁም የ20 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሥራም ከፕሮጀክቶቹ መካከል መሆኑን የዓዲግራት ከተማ ከንቲባ ሰሎሞን ሐጎስ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የልማት ፕሮጀክቶቹ አስተባባሪ ተክላይ ግርማይ እንዳሉት የልማት ፕሮጀክቶቹ ለ650 ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡

የልማት ፕሮጀክቶቹ የፊታችን ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑም ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.