Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እህልና አልሚ ምግብ እየተጓጓዘ ነው

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)በትግራይ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ23 ሺህ ኩንታል በላይ እህልና አልሚ ምግብ እየተጓጓዘ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ወደ ትግራይ ክልል ከትናንት ጀምሮ እያጓጓዘ ያለው እህልና አልሚ ምግብ ድሬዳዋ ከሚገኘው መጋዘን መሆኑን የኮሚሽኑ የሎጂስቲክስ አስተዳደር አመራር ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደምሴ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የተለያዩ ድርጅቶች እያደረጉት ከሚገኙት ድጋፍ በተጨማሪ መንግስት ድርጅቶቹ ባልደረሱባቸው 15 ወረዳዎች ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድሬዳዋ ከሚገኘው የእህል መጋዘን እህልና አልሚ ምግብ ማጓጓዝ መጀመሩን አስታውቀዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የፌዴራል መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን ዲያስፖራውንና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ለችግር የተጋለጡ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ እየተሰራ ነው።

መንግስት በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጊዚያዊነትና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኮሚሽኑ የዕለት ደራሽ ትራንስፖርት ስምሪት ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ዘመድኩን ታደሰ ÷ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚሰራጭ 23 ሺህ 309 ኩንታል እህል እየተጓጓዘ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.