የሥራ ዘመን እንዲገደብ የቀረበው አጀንዳ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ መሠረት የሚሆን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት የመቆያ ዘመን በሁለት የሥራ ዘመን እንዲገደብ የሚያደርግ አጀንዳ ለሀገራዊ ምክክር አቅርቧል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፥ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ብልጽግና ፓርቲ ይዞት ከሚቀርባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል አንዱ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን በሁለት የሥራ ዘመን ብቻ የመገደብ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ ውሳኔ በሀገሪቱ አስተማማኝ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት፣ የሰላማዊና ሕጋዊ የሥልጣን ሽግግር ባሕልን ለማስፈን እንዲሁም በሥልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ የመቀመጥ ፍላጎት የሚያስከትላቸውን የፖለቲካ ቀውሶች ከመሠረቱ ለመቅረፍ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያሉ ገዢዎች ሕገ መንግሥትና የተለያዩ አዋጆችን እያሻሻሉ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ማራዘም እንጂ፥ በተገደበ ጊዜ በፈቃዳቸው ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ለማስረከብ ሲወስኑ ተሰምቶ እንደማያውቅም ነው የጠቆሙት፡፡
ይህ ውሳኔ ለኢትዮጵያ የወደፊት የፖለቲካ ጤናማነትና መረጋጋት የሚጣል ታላቅ መሠረት መሆኑን ገልጸው፥ ርምጃው ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋችና በሕግ የበላይነት የምትመራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሀገሪቱ በሚካሄዱ ምርጫዎችና የፖለቲካ መድረኮች ላይ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችና ድምጾች በነጻነት እንዲሰሙ እንዲሁም የሕዝብ ውክልና ይበልጥ እንዲሰፋ ለማድረግ፥ ብልጽግና ፓርቲ በ15 በመቶ የምክር ቤት ወንበሮች ላይ አለመወዳደሩን አስታውሰዋል።
በዚህም በምክር ቤቱ 15 በመቶ የሚሆነውን ወንበር በፍጹም ፍላጎትና በነጻነት ለተፎካካሪዎች አሳልፎ የሚተውና ራሱን ከውድድር ውጪ ማድረግ በጥንካሬነት አንስተዋል።
ይህም ፓርቲው በሀገሪቱ እውነተኛ የብዙኃን ፓርቲ ሥርዓት እንዲገነባና የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅማቸው እንዲጎለብት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት