የፌዴሬሽን ም/ቤትና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ ለመሥራት ውይይት አካሄዱ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ ለመሥራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
መድረኩ በሰላም ግንባታ ሂደቶች፣ በግጭት አፈታትና በብሔራዊ መግባባት ላይ በሚታዩ ችግሮች ዙሪያ በመምከር የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን በምክር ቤቱ የማንነት፣ አሥተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ፍቅሬ አማን አስታውቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ የግጭት አፈታት እና የሰላም ግንባታ ሥራን በተመለከተ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ የአሠራር ማሻሻያ በማድረግ ዘመናዊና ባሕላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም ሥራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ተቋማቱ በሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ላይ በጋራ እና በተጠናከረ ቅንጅት መሥራታቸው ተልዕኮውን ውጤታማ እንደሚያደርገው መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከረይዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ለቅንጅታዊ ሥራ ስኬታማነት የአመራር ቁርጠኝነት፣ ጠንካራ ቅንጅት፣ በሙሉ አቅም መንቀሳቀስ ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩም የማስፈጸሚያ ዕቅድና የመግባቢያ ሠነድ ተዘጋጅቶ የተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት እንዲፈራረሙ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡