የትግራይን ሕዝብ ከሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን መታደግ ይገባል – የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ እና ኢትዮጵያን ለማዳከም ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር የትግራይን ሕዝብ ዳግም ወደ ጦርነት አዘቅት ለመክተት እየሠራ ይገኛል አሉ የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች።
ህገ ወጡ ቡድን ከሕገ-መንግሥቱ ውጭ የጦርነት ክተት በማወጅ ወጣቶችን እያስገደደ በመመልመል ላይ መሆኑንም አጋልጠዋል።
የቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፣ የትግራይ ሕዝብ ከዚህ በኋላ “ጦርነት በቃኝ” ማለቱን አፅንኦት ሰጥተዋል።
በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ ጄኔራሎች አቅሙ ኖሯቸው ሳይሆን፣ የልማት ሥራዎችን በማስተጓጎል እና በለመዱት ሁከት የግል ጥቅማቸውን ለማካበት ሲሉ ብቻ የጦርነት ወሬ እንደሚነዙ መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ጄኔራል ሳሞራ፣ ‘ፅምዶ’ ስለተባለው አደረጃጀት ሲያብራሩ፤ ይህ በግብጽ የሚመራ እና በሻዕቢያ የተቀነባበረ የጥፋት ተልዕኮ መሆኑን አስረድተዋል።
ሻዕቢያ ለትግራይ ሕዝብ እውነተኛ ወዳጅ ቢሆን ኖሮ በጉልበት የያዛቸውን እንደ ዛላምበሳ እና ኢሮብ ያሉ ቦታዎችን በለቀቀ ነበር ብለዋል።
ይህን እውነት እያወቀ ህገ ወጡ ቡድን ከሻዕቢያ ጋር ጥምረት መፍጠሩ የድንቁርና ማሳያ እና ሕዝቡን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አብራርተዋል።
ማንኛውም የፖለቲካ ልዩነት መፈታት ያለበት በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የቀድሞ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንን ኮሎኔል ገብረዋህድ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ቡድኑ ለሕዝቡ የዴሞክራሲ እና የፍትሕ ጥያቄ ደንታ እንደሌለው አስረድተዋል።
ሕገ ወጡ ቡድን “ለሕዝብ ቆሜያለሁ” የሚለው ጭምብል ሥልጣንን ለማራዘም እና ሀብት ለማካበት የሚጠቀምበት ማታለያ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዚህ የቡድኑ ራስ ወዳድነት የተነሣም፣ የትግራይ ሕዝብ “የቀሩት ልጆቻችን ያልቃሉ” በሚል ስጋት በሕይወት እና በሞት መካከል እንዲኖር መደረጉን ጠቁመዋል።
በመሆኑም እነዚህ ለሥልጣን የቋመጡ አካላት ተወግደው በክልሉ እውነተኛ ፍትሕ እና ለውጥ ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሁለቱ አንጋፋ የጦር መኮንኖች የፌዴራል መንግሥቱ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እና በረጋ መንፈስ ለመፍታት የሚያደርገው የትዕግሥት አካሄድ እጅግ ጠቃሚ እና ተመራጭነት ያለው መሆኑን አድንቀዋል።
በትግራይ ክልል በዚህ ሕገ ወጥ ቡድን እየደረሰ ያለው መከራ፣ እንግልት እና የጦርነት ስጋት አሁን ላይ በቃ ሊባል እና የትግራይን ሕዝብ ከዚህ አጥፊ ቡድን መታደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።