Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለቀጠናዊ መረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ ውህደት በቁርጠኝነት ትሰራለች – አምባሳደር ታዬ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለቀጠናዊ መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት በቁርጠኝነት ትሰራለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ተናገሩ፡፡

በ44ኛው የአፍሪካ ህብረት የአስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አምባሳደር ታዬ እንደተናገሩት÷ የህብረቱ ጉባኤ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ አስተምህሮ በሚል መሪ ሃሳብ ትኩረቱን አድርጎ መወያየት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

በመድረኩ የማይበገር የትምህርት ሥርዓት መገንባት እና በመላው አፍሪካውያን የሚገኙ ህፃናት ጥራት ያለው የትምህርት አግልግሎት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ በዚሀም በሀገር አቀፍ የተማሪዎች ምግባ ፕሮግራም ከ6 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን መንግስት እየመገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት አምስት አመታት መንግስት የህዝብ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እና የርቀት ትምህርት ቤቶችን ቁጥር በማሳደግ አካታች እና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲጨምር ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ሀገራት 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ አስተምህሮ በሚለው መሪ ሀሳብ ህብረቱ እንዲመክር እና አባል ሀገራቱ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ቀልጣፋ እና የማይበገር የትምህርት ስርዓትን ለማስፈን እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ እድገት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም÷ አፍሪካ ከቡድን 20 አባል ሀገራት እና ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በትብብር ልትሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

አፍሪካ ከቡድን 20 አባል ሀገራት ጋር በሚኖራት ትብብር የአህጉሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሚና እንደሚኖረው እና በተመሳሳይ አፍሪካ ከብሪክስ ጋር በትብብር መስራቷ የደቡብ ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አጀንዳ 2063 የአፍሪካውያን የጋራ የእድገት ራዕይ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ÷ ራዕዩን ለማሳከት ጠንካራ ትብብር እንዲሁም የፖለቲካ ቁርጠኝንት አስፈላጊ መሆኑንን አብራርተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.